በቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
በእድሜ ትንሹና ገና ከመምጣቱ የህዝብን ትኩረት ለማግኘት የበቃው ሠማያዊ ፓርቲ በተለይም ከአንድነትና መኢአድ ሁለት ሁለት ቦታ መሰንጠቅ በኋላ ጎልቶ የመታየት ቀለሙ ይበልጥ የደመቀ ይመስላል ። ፓርቲው ከየት ተነስቶ እስከምን ይጓዛል ? የሚለውን ጥያቄ ከወቅታዊ ሁነቶች ጋር በማዛመድ የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከሆነው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ጋር 1:50 ሰዓት የፈጀ ቃለመጠይቅ አካሂደናል ። በፌስ ቡክ የደረሱኝንና ሌሎች ጥያቄዎችን አንስቻለሁ
ኢትዮዴይሊፖስት -ሰማያዊ ፓርቲ ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ የተቋቋመው መቼ ነው ?
አቶ ዮናታን – 2004 ዓ.ም ታህሳስ ወር ጠቅላላ ጉባኤውን አድርጎ በይፋ መመስረቱን አውጇል ። ምርጫ ቦርድ እውቅና ሰጥቶ የመዘገበው ግን ሐምሌ /2004 ዓ.ም ነው ።
Yonatan Tesfaye
ኢትዮዴይሊፖስት – ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች እያሉ ሰማያዊ ፓርቲ ለምን ተቋቋመ ? ቁጥሩን በአንድ ከመጨመር ባለፈ ሌሎች ያልሰሩትን ምን የመሰራት አላማ ኖሮት ነው?
አቶ ዮናታን – ከምርጫ 97 በኋላ የነበረውን የፖለቲካ ድብታ ሁሉም ሰው የሚረሳው አይደለም ። ከዚያ በኋላ የነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች በ3 አይነት የተዋቀሩ ናቸው ። በዶ/ር መረራ የሚመራው ህብረት በነበረበት ቀጥሏል፡፡ ቅንጅት ለሁለት ተከፍሎ አንዱ ትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ ወስዶ ከሀገር ወጥቷል፡፡ ሶስተኛው ደግሞ እነ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲን መስርተው የቻሉትን ያህል ሰላማዊ ትግሉን ለማስቀጠል ተንቀሳቅሰው ነበር ። በእነዚህ መካከል ግን የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ ድብታ ውስጥ የከተተው የህብረተሰብ ክፍል ነበር ። ያን ድብታ የሚገፍ ሀይል ያስፈልግ ነበር ። ፖለቲካው ለኢህአዴግ የጎሳ ፖለቲካ እጅ የሰጠ የሚመስልበት ሁኔታ ነበር ። እነዚህንና ሌሎች ምክንያቶችን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የአዲሱን ትውልድ ጥያቄ ሊያስተጋባ የሚችል ፣ ዘመኑን የሚዋጅ፣ የፖለቲካ ድብታውን ሰብሮ ሊወጣ የሚችል የፖለቲካ ሀይል ያስፈልግ ነበር ። በዚያ ውስጥ ነው የተፈጠርነው ።
ኢትዮዴይሊፖስት – የምርጫ ወቅት ነውና ስለእሱ እናውራ ። በምርጫ ላይ ያላችሁ አቋም ምንድንው ? በፌስቡክ የደረሱኝ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች በምርጫ ገዢውን ግንባር ከስልጣን ማውረድ ይቻላል ብላችሁ ታምናላችሁ ? የሚል ነው ። በእግርጥ ታምናላችሁ ?
አቶዮናታን – አናምንም ።
ኢትዮዴይሊፖስት – ካላመናችሁ ለምን በምርጫ ትወዳደራላችሁ?
አቶዮናታን – የሰማያዊ ፓርቲ ትልቁ ግብ ሕዝቡ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ነው ። ሕዝቡ የስልጣን ባለቤት ሆነ ማለት ነጻነት አለው ማለት ነው ። ዲሞክራሲያዊ መብቱ ተከበረ ማለት ነው ። ወደ ምርጫው የገባነው የዋህ ሆነን አይደለም ። ኢሕአዴግ በምርጫ ይወርዳል የሚል ቀቢፀ ተስፋ ውስጥም አልገባንም ። የፓርላማ ወንበር አግኝተን ተመቻምቸን እንቀጥላለን የሚል ሀሳብ ውስጥም አልገባንም ። ግን ምርጫ ሰላማዊ ትግል በመደገፍ ረገድ ትልቅ አቅም ይኖረዋል ። እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ መወዳደር ፣ ለማሸነፍ መጣር ቢኖርም ትግላችን ከአገዛዝ ወደ ነጻነት መሆኑን ማንም አይስተውም ።
ኢትዮዴይሊፖስት – “ጉዟችን ከአገዛዝ ወደ ነጻነት ነው” ካላችሁ፣ ኢሕአዲግ በምርጫ ስልጣን ይለቃል የሚል የዋህነት ከሌላችሁ፣ የጦር መሳሪያ አንስተው ነጻነትን በጠመንጃ ሊያገኙ የሚሞክሩ ሀይሎችንም ካልደገፋችሁ በየትኛውም መንገድ ነው ከአገዛዝ ወደ ነጻነት የምትጓዙት?
አቶዮናታን – በየትኛውም መንገድ ሊሳካ ይችላል። ሂደቱ ነው የሚወስነው ። የቱም ቢሆን ረጅም ጊዜ ይወስዳል ።ትጥቅ ትግሉ እንደውም ከሰላማዊ ትግሉ የበለጠ ረጅም ጊዜ ይወስዳል ። ምክንያቱም የምትከፍላቸው ዋጋዎች ይበዛሉ ። በሀገርህ ልትደራደርባት ሁሉ ትችላለህ ። ሕወሓት ሀገራችንን ይህን አይነት ዋጋ አስከፍሏታል ። ከኤርትራ መገንጠል ጀምሮ አሰብን ማጣት ፣ ባድመ ላይ ሕይወት መክፈል ፣ በአለም አቀፍ ፖለቲካውም ላይ የከፈልነው ዋጋ አለ በትጥቅ ትግሉ ምክንያት ። አሁንም በዚያ መንገድ የሄዱ ሀይሎች ይህን ሁሉ አገናዝበው እንዲሆን ተስፋ አለኝ ።
ሰማያዊ ፖርቲ እንደ የፖለቲካ ፓርቲ ሰላማዊ ትግሉ ላይ ተጣብቆ ፣ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍሎ ፣ የሄደውን መንገድ ሁሉ ሄዶ ከግብ እንዲደርስ እናደርጋለን ስንል ዋናው ግባችን ሕዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን እስከዛሬ ከሄድንበት የተለየ መንገድ መሄድ አለብን ፡፡ሰላማዊ ትግል ኢትዮጵያ ውስጥ አልተሞከረም ። የፓርቲ ፖለቲካ ነው ያለው ። በብዛት ቢሮ ውስጥ ከመቀመጥ ያለፈ አልተሰራም ። ሰማያዊ ፖርቲ የተለየ መንገድ እከተላለሁ ሲል እነዚህንና በአለም የተካሄዱ ሰላማዊ ትግሎችን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አዛምዶ ነው ።
ኢትዮዴይሊፖስት – የምርጫን ፖለቲካ እንደኪሳራ ቆጥረው ነፍጥ ያነሱ ሀይሎች አሉ ። እናንተ ደግሞ በምርጫ የስርአት ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል አያመናችሁም ሰላማዊ ትግል የተባለ ሌላ አማራጭ አለ እያላችሁ ነው ። የእናንተ አማራጭ ከባለጠመንጃዎቹ የተሻለ መሆኑን አስረዳን እስቲ ።
አቶዮናታን – እኛ ከምርጫና ከጠመንጃ ፣ ከጠመንጃና ከሰላማዊ ትግል የቱ ይበልጣል? የሚለው ክርክር ውስጥ አንገባም ። ነባራዊ ሁኔታውን ማየት ግን የተሻለ ነው ። ደርግ ንጉሡን ገልብጦ በጠመንጃ ስልጣን ያዘ ። ራሱ ደርግም የወረዳው በጠመንጃ ነው ። ኢሕአዴግም በጠመንጃ ስልጣን ይዞ ምርጫ የሚባል የጨዋታ ሜዳ አበጅቶ አልወርድም ነው ያለው ። ኢሕአዴግ በጠመንጃ ቢወርድም መጪው ያለጠመንጃ ለመውረዱ ዋስትና የለም ። የሰላማዊ ትግል አማራጭ ግን ሕዝቡን የስልጣን ባለቤት የሚያደርግ ነው ፡፡
Yonatan Tesfaye
ኢትዮዴይሊፖስት – አሁንም እኮ ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ሆነ እየተባለ ነው ።
አቶዮናታን – ልክ ነህ ይባላል ። ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ቢሆን ግን በጋምቤላ ፣ በኦሮሚያ ፣ በሶማሌ፣ በአማራው አካባቢ ያሉ አይነት ግጭቶች ውስጥ አይገባም ። ይሁንናም ግን በሰላማዊ ትግል የሚመጣ ስልጣን “እምቢኝ አሻፈረኝ ፤ከተቀመጥኩበት ወንበር አልነሳም” ለማለት አይመችም ። ወደ ስልጣን መውጫ ብቻ ሳይሆን መውረጃውንም ቀድሞ ያበጀ ስርዓት ነው የሚመጣው ። ኢሕአዴግን በሰላማዊ ትግል ከስልጣን ያወረደ ሕዝብ ቀጣዩንም በተመሳሳይ ለማውረድ የሚከለክለው ሀይል አይኖርም ። በ1997 ትልቅ ንቅናቄ ተፈጥሯል፡፡ ግን በትግል የመጣ አልነበረምና ካሸፈ ። ሕዝብ በትግል መውጣት አለበት ። የግድ በሚሊዮኖች መቆጠር የለበትም ።አምስትና አስር ሺህ ሆኖም በህዝብ የበላይነት ፣ በሕግ የበላይነት ስርዓቱን እየፈተነ ፣ የስርዓቱን አገልጋዮች እያሸመደመደ ምንም ማድረግ እንዳይችሉ ምክንያት የሚያሳጣ ሀይል መፍጠር ይችላል ። ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተሞከረም ። በ1997 ያን ያህል ሕዝብ አይተን እንደረካነው አሁን ደግሞ በትግል ራሱን ችሎ የሚመጣ ሀይል እንፍጠር ነው አያልን ያለነው ። ሰላማዊ ትግል ሲባል ፖለቲካና ፓርቲ ላይ የታሰረ ይመስላል ፡፡ አይደለም ። ምንም እንኳን የፖለቲካ ሀይሉ እነዚያን ጥያቄዎች ቢያሳነም ብዙ ሰው ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ሳይገባ ፣ በትግሉ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል ፡፡
ኢትዮዴይሊፖስት – የምርጫና ጠመንጃ ትግል መዳረሻቸው ይታወቃል ። የሰላማዊ ትግል መዳረሻስ ምንድነው ?
አቶዮናታን – መወሰን አይቻልም ። ምናልባት በሕዝብም ሀይል ፣ በዲፕሎማሲም ፣ በአጠቃላይ በዲሞክራሲ ሀይሎች ግፊት አስገድደን ሊወድቅ ይችላል ። ሰላማዊ የሽግግር ሀይል ሊቋቋም ይችላል ። አብዮት ሊነሳ ይችላል ። ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሊነሳ ይችላል ። መገመት አይቻልም ። እዚያ ጫፍ ላይ ከመድረሱ በፊት ግን ሕዝቡ መንቃት አለበት ። እንደሚችል ማሳየት መቻል አለብን ።ህዝቡ ነጻ አውጪዎችን መጠበቅ ሳይሆን ራሱን ነጻ መውጣት አለበት ። ይህን ማድረግ እንደሚችል ግን ቀድሞ ግንዛቤን ማዳበር ያስፈልጋል ፡፡
ኢትዮዴይሊፖስት – ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ አንጻር ሰላማዊ ትግል ከምርጫም ሆነ ከጠመንጃ ትግል የተሻለ ውጤታማ የሚያደርገው ምን አለ ?
አቶ ዮናታን – በምርጫው ለውጥ ማምጣትን የተካ የተሻለ የዲሞክራሲ ስርዓት የለም ። በምርጫ ለውጥ ማምጣት ሲያቅት ፣ ስልጣን የያዘው አካል ምርጫው ነጻ እንዳይሆን ሊያደርግና ለምርጫ ሕግ አልገዛ ሲል ነው ወደ ጠመንጃም ሆነ ሰላማዊ ትግል የሚገባው ። ሰላማዊ ትግልም ሆነ የጠመንጃው ትግል በአንዳንድ ቦታ ውጤታማ ላይሆኑ ይችላሉ ። ይህ የሚሆነው አምባገነን የሚባሉትና የዲሞክራሲ መብት የሚጥሱት መንግስታት ለሕዝቡ የተሻለ ቁሳዊ ሕይወት የሚሰጡበት ሁኔታ አለ ። ለምሳሌ እነቻይናና ኢንዶኔዢያን ማየት ይቻላል ፡፡ስለዚህ ምንም እንኳ ለውጥና መደብለ ፓርቲ ስርዓት ብትፈልግ እንኳ ትግሉን የሚገዳደር ቁሳዊ እድገት ስላለ ይህ ለጊዜውም ቢሆን ውጤቱን ሊያኮላሸው ወይም ትግሉን ሊያራዝመው ይችላል ፡፡
ኢትዮዴይሊፖስት – ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይስ ?
አቶ ዮናታን – ወደ እሱ ልመጣልህ ነው ። ሀገራችን በጣም አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው እየገባች ያለችው ። ለልጅ ልጆቻችን የምናወርሰው ብድር በጣም ጣራ እየነካ ነው ። አሁን ያለብን ከፍተኛ ችግር የሚተመንም አይደለም ።የሀይማኖት ችግር አለ ። ሙስሊሞቹ በንቃት ስለሚታገሉት የእነሱ ጎላ እንጂ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ( ማህበረቅዱሳን ) ውስጥ የተፈጠረውን ችግር እናስታውሳለን ። የሀገር ውስጥና የውጭ የተባሉ ሁለት ሲኖዶሶች አሉ ። ሙስና በቤተክርስቲያን ውስጥ በጣም ተስፋፍቷል ። ይህ እየተስፋፋ ሲመጣ ህብረተሰብ የለውጥ ሂደት ውስጥ መግባቱ አይቀርም ።
በኢኮኖሚው ያለውን ችግር ስታየው ከጊዜ ወደ ጊዜ የደሀው ቁጥር በጣም እየጨመረ ፣ ከሀብታሙ ጋር ያለው ልዩነት እጅግ እየሰፋ ነው ። የስራ አጡ ቁጥር ከልክ እያለፈ ፣ የትምህርት ስርዓቱ የድህነትና ስራ አጥነት መጠኑን እያስፋፋው ነው ። አብዛኛው ስራ መፍጠር ሳይሆን ተዛዥ ሆኖ እንዲወጣ የሚያደርግ የትምህርት ስርዓት ነው ያለው ። ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡት ትራንስፖርት ፣ መብራት ፣ ውሃ ፣ ስልክ በሙሉ እየወደቁ ነው ። ከእነዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የኢሕአዴግ ከጥንት ጀምሮ የነበረና አሁንም ድረስ የሕዝብ ተቀባይነት ያላስገኘለት ሀገራዊ እይታ አለ ። ለኢትዮጵያ ያለው ክብር ኢሕአዴግ የሚታወቀው ባንዲን በማራከስና ጨርቅ ነው በማለት ነው ። ከዚያ የባንዲራ ቀን ብለው ቢጀምሩም ቅቡልነቱን አላገኙትም ። እነዚህ ሁሉ ችግሮች እየባሱ እንጂ እየረገቡ አልመጡም ። ስለዚህ የእኛ ጥያቄ ማንሳት በራሱ ሳይሆን ለውጡን የሚያመጣው የገዢው ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣት ነው ። ከስህተቱ መማር አለመቻሉም ነው ፡፡
በሰብአዊ መብት ላይ ያለው ደግሞ ሁሉንም ይነካል ። ፖለቲከኞች ታሰሩ ፤ ዝም ተባለ ። የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊዎች በገፍ ታሰሩ ፤ ሕዝቡ ዝም አለ ፡፡ በድረገጽ ያገባናል ብለው የሚጦምሩ ወጣቶች ታሰሩ ። ጋዜጠኞች ተሰደዱ ። ጋዜጦች ተዘጉ ። አፈናው አየሰፋ ሲሄድ ሕዝቡን ወደ ትግሉ ይቀላቅሉታል ። አሁን ላይ የሚታዩ ነገሮች ባይኖሩም ችግሮቹ እየሰፉ ሲሄዱና እንደ ፖለቲካ ሀይል ግፊት ስታደርግ አንድ እርምጃ ወደፊት ይሆናል ። የሁሉም የዲሞክራሲ ሀይሎች የመጨረሻ ግብ ተመሳሳይ ነው ። ሕዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ነው ። በንጉሱ ጊዜ የነበረው ጥያቄ አሁንም አለ፡፡ ጥያቄውን ደግሞ ኢሕአዴግም አልመለሰውም ። እስኪመለስ ይቀጥላል ። መልሱ በማንኛውም መንገድ ሊመጣ ይችላል ። ግን ዘላቂ ውጤት የሚኖረው በሰላማዊ ( ነፍጥ አልባ ) ትግል ሲመጣ ነው ፡፡ ሕዝቡ ላይ “ይቻላል!” የሚለውን ስሜት መፍጠር እንጂ ኢህአዴግ በየትኛውም መንገድ የደከመ ድርጅት ነው ።
ኢትዮዴይሊፖስት – ብዙዎቹን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያመሳስላቸው የምርጫ ሰሞን ከያሉበት ብቅ ብቅ በማለት ድምጻቸውን ማሰማት ፣ በምርጫው ሳይቃናቸው ሲቀር ወደ መፍረስø ድንዛዜ መግባትና ቀጣዩን አምስት አመት መጠበቅ ነው ። ከዚህ አንጻር ሰማያዊ ፓርቲ በ2007 ምርጫ አንድም የምክር ቤትና የክልል ወንበር ባያገኝ ፣ አንድም አባሉ ባይመረጥ ከምርጫው በኋላ የሚኖረው አቋም ምን ይሆናል?
አቶዮናታን – ጥሩ ጥያቄ ነው ። እንደውም ሰማያዊ ፓርቲ የተመሰረተበት ምክንያት ይሄ ነው ።
ኢትዮዴይሊፖስት – የቱ ምክንያት ?
አቶ ዮናታን – እስከዛሬ የነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ተወስነው አንድ ሁኔታ ሲከሰት መግለጫ ከማውጣት ያለፈ ፋይዳ ያልነበራቸው ነበሩ ። ይህን ስል ግን የተቃዋሚዎች ድክመት ብቻ አይደለም ። ገዢው ስርዓትም መንገዱን ዘግቶታል ። የተዘጋውን ለማስከፈትና ሕዝቡ ጋር ለመድረስ ግን መታገል ያለብን እኛ ነን ።ስለዚህ ሰማያዊ ፓርቲ ሲመሰረትም ይህን አሳካለሁ ብሎ ነው ። ሰማያዊ ፓርቲ በብርቱ መንቀሳቀስ የጀመረው አሁን ምርጫው ሲመጣ አይደለም ። ገና ከመሰረቱ ጀምሮ ነው ዋጋ መክፈል የጀመረው ። አሁን የምናደርገው ትግል መቀመጫ ለማግኘት አይደለም ። ትልቁ ትኩረታችንም አይደለም ።
ኢትዮዴይሊፖስት – መቀመጫ ለማግኘት የማይታገል ምርጫ ተወዳዳሪ አለ ?
አቶዮናታን – በሂደቱ ውስጥ ሕዝቡ ጋር መድረስ ባለብን መጠን መድረስ ነው ዋና ጉዳያችን ። ኢ/ር ያልቃል ከምርጫ ሲሰረዝ “ትልቁን አላማዬን ተነጠቅሁ” የሚል ስሜት አልነበረውም ። በፊቱንም ጓጉቶ አልነበረም የተመዘገበው ። ማንም የፓርቲያችን አባል ለመመረጥ ጉጉት ያለው አይመስለኝም ። ስንመዘገብም “ይቻላል !” የሚለውን የለውጥ መንፈስ በሁለት እግሩ ለማቆም ነው ድካምና ልፋታችን:: እንደ ፖለቲካ ፖርቲ ይህን ያህል ወንበር አገኛለሁ ብለህ ልታቅድ ትችላለህ ። ፖለቲካው ላይ ለወጥ የሚያመጣው ግን ሁለትና አስር ወንበር ማግኘቱ ባለመሆኑ ምርጫው ሲያልፍም አሁን ባለንበት ሁኔታ የምንቀጥል ይሆናል ፡፡
ኢትዮ ዴይሊ ፖስት ከአቶ ዮናታን ጋር ያደረገውን ቃለመጠይቅ ቀጣይ ክፍል
-ግን አቶ ዮናታን የባቡር መንገዱ ላይ የመኪናዎች አደጋ መብዛት የኢሕአዴግ ችግር ነው እንዴ የአሽከርካሪው ጥፋት ለምን አይሆንም የመኪና መሄዳ መንገድ እያለ የባቡር አጥር ላይ መውጣታቸው ለምን የመንግስት ችግር ይሆናል
– ሰማያዊ ፖርቲ የዛሬ 24 አመት ስልጣን ይዞ ቢሆን ኖሮ አሁን በሀገሪቱ ካለው ሁኔታ የትኛዎቹ እንዳይኖሩ ወይም እንዲኖሩ ያደርግ ነበገር የሚል ነው
-በአንዳንዶች አስተያየት አሁን ያለው ሰማያዊ ፓርቲ ምንም ስልጣን ላይኖረው እንኳ ለተቃዋሚዎች እልቅና አይሰጥም ተቃዋሚዎች ብዙም ለውጥ እንደሚያመጡና እሱ ብቻ የለውጥ ባለቤት እንደሆነ ያስባል የሚል ትችት ያቀርብባችኋል ስለዚህ ይህ ፓርቲ ስልጣን ቢኖረውና ጠመንጃ ፖሊ ደህንነት ቢኖረው ጭራሽ ወደ አምባገነንነት ይሄል የሚል ጥርጣሬ ያላቸው ጥቂት አይደሉም ይህን ሀሳብ በምን ታስተባብለዋለህ ፡፡
– ሰማያዊ ፓርቲን ከግንቦት 7 ከድምጻችን ይሰማ እና ከሙስሊሙ እንቅስቃሴ ጋር አያይዘው የሚያስቡ አሉ በተለይም የሙስሊሙ እንቅስቃሴ ደማቅ ስለሆነ ሰማያዊ ፖርቲ ራሱን ማስተዋወቂያና የሙስሊሙ ወገንተኛ አድርጎ ተጠቅሞበታል የሚሉ አሰብ ያንተ ምላሽ ምንድነው
– አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና የፕሬስ ውጤቶች ውጭ ሀገር ለሚሄ ሰዎች የመኖሪያ ፍቃድ እንዲያገኙ አባላቸው እንደሆኑና ገዢው ግንባር ተጽእኖ እንዲደረግባቸው የሚገልጽ ሀሰተኛ ደብዳቤ በመጻፍና መታወቂያ በመስጠት ከፍተኛ ገቢ ያገኛሉ ሰማያዊ ፖርቲ ለአንድም ሰው ቢሆን መታወቂያ ላለመሸጡ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይችላል
እነዚህን እና ሌሎች ጥያቄወችን በሚቀጥለው ሳምንት ይዘንላቹ እንቀርባለን።
http://ethioforum.org/amharic/%E1%88%85%E1%8B%9D%E1%89%A1-%E1%8A%90%E1%8C%BB-%E1%8A%A0%E1%8B%8D%E1%8C%AA%E1%8B%8E%E1%89%BD%E1%8A%95-%E1%88%98%E1%8C%A0%E1%89%A0%E1%89%85-%E1%88%B3%E1%8B%AD%E1%88%86%E1%8A%95-%E1%88%AB%E1%88%B1/