Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) – በጋራ ላለመስራት ማንገራገር እና አለመፈለግ እና በስሜት መነዳት የፖለቲካ ውጤቱ እና ጠቀሜታው ለጋራ ጠላታችን ለወያኔ ነው::የተቃዋሚ ሃይሎች ጥንካሬ እንዲጎለብት በየድርጅቱ ውስጥ ያሉትን እንከኖች በማጥራት በጋራ እና በተመቻቸ የሃሳብ መግባባት ተቻችሉ እና ተግባብቶ የትግል ስትራቴጂን ግብ ለማድረስ ለአንድ ወጥ ህዝባዊ እና ሃገራዊ አጀንዳ ተግቶ መስራት ይጠበቅብናል።ባሳለፍነው የትግል አመታት ውስጥ የተቃዋሚዎች እርስ በ እርስ መፈራረጅ መወነጃጀል መናናቅ ለስልጣን ጥመኝነት መሮጥ እንዲሁም ለስም እና ለዝና መትጋት ያለመደማመጥ እና ያለመከባበር ፖለቲካ ተቀራርቦ ያለመነጋገር እና ያለመመካከር ፖለቲካ ሃገራዊ ሆደሰፊነት እና መቻቻልን ያላዘለ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተረፈው ነገር ቢኖር ከጭቆን ወደ ጭቆና ማቅ ውስጥ ከመዘፈቅ ውጪ ምንም የናፈቀውን የነጻነት አየር እንዲተነፍስ አላደረግነውም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል። ይህ ሳይታለም የተፈታ እና የሁሉም የነጻነት ፈላጊ ሃይሎች ጥያቄ ነው። በሃገር ውስጥ ያሉትን ፓርቲዎች መዋቅሮቻቸውን በማጠናከር የውስጥ ድክመቶቻቸውን በመቅረፍ እንዲጠነክሩ የማድረግ ግዴታ ከለውጥ ፈላጊ ሃይሎች ይጠበቃል። መመካከር መተራረም ግድ ይላል። በውጪው አለም የሚገኙ የነጻነት እና የለውጥ ሃይሎች እንዲጠናከሩ እና ከጥልፍልፎሽ ፖለቲካ ወተው ጠንካራ ሃይል እንዲሆኑ የዲያስፖራው ሃይል ከበፊቱ በበለጠ መልኩ ሊሰራ ግድ ይለዋል። የወያኔ የጎን ውጋት እና የራስ ምታት የሆነው ዲያስፖራው የጀመረውን የትግል ስልት እና ትጋት በማስፋት ሚዲያዎችን በማጠናከር እና የነጻ አውጪ ፓርቲዎችን በመርዳት በማግባባት ጠንካራ ሰንሰለት ከሃገር ቤት ጋር በመፍጠር ሕዝብን ከጨቋኞች ነጻ ማውጣት አለበት።ዲያስፖራው በየቀኑ ወያኔ የሚፈጥረውን ተራ የቤት ስራ እና የማደናገሪያ ማዘናጊያ አሉባልታ ፊት ሳይሰጠው በለውጡ ጉዳይ ላይ በማተኮር በሃገር ቤት ያለው ሃይል እንዲስማማ የፖለቲካ ጡዘቶች ክፍተት እንዳይኖር ተቀራርቦ እንዲሰራ ትልቁን ሚና መጫወት አለበት::
ወያኔ የተቃዋሚዎችን እና የለውጥ ሃይሎችን እርስ በእርስ መፈነካከት በማየት አርጩሜውን ተስፋ በሚጣልባቸው ግለሰቦች እና ፓርቲዎች ላይ እያወናጨፈ ባለበት እንዲሁም የውስጥ አሰራራቸውን በመሰለል በትግሉ ውስጥ ያላቸውን ሚና እንዲኮላሽ በመስራት የውስጥ ድክመቶቻቸውን በመጠቀም እርስ በርስ እንዲፋጁ እና ተቃዋሚዎች እንዲከስሙ ጥንካሪያቸውን እንዳያገኙ ሲሰራ ይህንን እንዴት አድርገን በማሻሻል የወያኔን ሴራ ማክሸፍ አለብን የሚል አመኔታ የሚያስገኝ ሕዝባዊ ስራዎችን በመስራት ጥንካሬን ማግነት እንዲሁም ሕዝባዊ ድጋፎችን ማግኘት ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ መሆናቸውን ተቃዋሚዎች ሊያውቁት ይገባል::ተቃዋሚዎች ካለፈው ድክመቶቻችን ተምረን ከዘለፋ እና ከስድብ እንዲሁም ከመፈራረጅ የሴራ ፖለቲካ በመውጣት ጥንካሬዎቻችንን የምናሳይበት ለውጥ የምናመጣበት አመት እንዲሆን በጋራ ጠንክረን መስራት አለብን።አንድነት ሃይል ነው የሚለው ብሂል ለሃገራዊ አጀንዳ መተግበር ትልቅ አስታውጾ አለው::ከኛ በላይ ላሳር ከኛ በላይ አዋቂ የለም የሚል አመለካከት ይዞ ከመክነፍ የህዝብን ጥያቄ መሰረት አድርጎ ተቀራርቦ በመነጋገር እና በመወያየት ሃገራዊ ማኒፌስቶ በማምጣት የጋራ ሃገራዊ አጀንዳ በመቅረጽ ለለውጥ መትጋት ግዴታ ነው::
የሚዲያ ተቋማት እና የድህረገጽ ውጤቶች ሕዝብን በማስተማር ሕዝብን መብቱን እና ነጻነቱን አውቆ ለሌላው እንዲያስተምር በማድረግ ረገድ አስፈላጊውን ወቅታዊ መረጃ እና መነሳሳትን በማስረጽ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል። ያለፉ እና የከሰሙ ወሬዎችን እና አሉባልታዎችን ከመርጨት የወያኔ የፈጠራ አደናባሪ እና አዘናጊ አጀንዳዎችን እኝኝ በማለት ከማውራት ብሄር ተኮር ክፋፋይ ሃሳቦችን ከማርከፍከፍ አዛኝ መሳይ መርዝ ሃሳቦችን ከመናገር ተቆጥበን ሕዝቡን ስለመብቱ እና ነጻነቱን በማስተማር ረገድ መትጋት ከተያዘ ለውጥ የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለም። ትችትን እና ሂስን ላለመዋጥ እውነትን ላለመቀበል የሚደረጉ ሩጫዎች ታጥቦ ጭቃ እንጂ የትም እንደማያደርሱ እንዲሁም ፓርቲዎችን እና ሰዎችን መፈረጅ እና መወንጀል ሃሳቦችን ማጣጣል ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ካለፈው ተምረናል ። ያሳልፍነው የትግል ሂደት ከጭብጨባ እና ስብሰባ ያለፈ ፋይዳ እንዳሌለው ተገንዝበን የወሬ እና ሆይሆይ ትግል ስለማያዋጣ ጥንካሬን እና ለውጥን የምናመጣበትን የትግል ስልት በመመካከር በመከባበር እና በመወያየት ሃሳብን በማቻቻል መረጃ በመለዋወጥ ሃገራዊ የጋራ አጀንዳ ሊኖረን ይገባል እላለሁ። #ምንሊክሳልሳዊ
http://www.mereja.com/amharic/467436
No comments:
Post a Comment