Opposition Voice

Opposition Voice

Saturday, March 28, 2015

የልማታዊ” እና “ሁለገብ” ጋዜጠኞች አንድም ፣ ሁለትነትም – ያሬድ ኃይለማርያም




ጋዜጠኝነት ትልቅ ክብር የሚሰጠው፣ የራሱ የሆነ መርህና ስነ-ምግባር ያለው፣ ጠያቂነትን ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትንም በውስጡ የያዘ የሙያ መስክ ነው። ለዛም ነው ጋዜጠኛ የሕዝብ አንደበት፣ አይንና ጆሮ ነው የሚባለው። ሕዝብ በሚከበርበት ቦታ ሁሉ ጋዜጠኛም ይከበራል። ሕዝብ በሚዋረድበት፣ በሚታፈንበትና በሚዋከብበት ስፍራም ጋዜጠኛ ይዋረዳል፣ ይሳደዳል፣ ይታፈናል፣ ይዋከባል፣ ይታሰራል፣ ሲከፋም ይገደላል። ይህም በሕዝብ፣ በመንግሥትና በጋዜጠኛ መካከል ያለውን ቁርኝት በደንብ ያሳያል። ሕዝብና መንግሥት ልብ ለልብ ሊገናኙ የሚችሉት ጋዜጠኛ ሲኖር ነው። የሁለቱን የልብ ትርታ እያደመጠና ያንዱን ላንዱ እያስደመጠ በመካከላቸው ገደል እንዳይኖር ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።
ጋዜጠኞች ይህን ታላቅ ኃላፊነት ለመወጣት ከሚጠበቅባችው ነገሮች ዋነኛውና መሰረታዊው ነገር የሙያውን ሥነ-ምግባርና መርሆዎች ጠንቅቆ ማወቅና ለመተግበርም መጣር ነው። በዚህ ሙያ ላይ የተሰማራ ሰው ምንም ያህል በሙያው ቢሰለጥንና ቢመራመር ከመርሆቹና ከሥነ-ምግባሩ በራቀ ቁጥር ከላይ የተጠቀሰውን አሉታዊ ሚና ከመጫዎት ይልቅ ለሚኖርበት ማኀበረሰብ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ዋነኛ ጠንቅ ይሆናል። የጋዜጠኝነት ሙያ አንድን ማኅበረሰብ በሚዘረጋው የመረጃ መረብ የማዋሃድና የማቀራረብ ኃይል ያልውን ያህል በሥነ-ምግባር ብልሹዎች እጅ ሲወድቅ ደግሞ እንደ ኒውክለር ቦንብ ሕዝብን የማፋጀትና ለከፋ እልቂት የመዳረግም አቅምም አለው። ለዚህም የሩዋንዳዉን የዘር እልቂት ያፋፋሙትን የአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ልብ ይሉዋል። አንድ ሰው በጋዜጠኝነት ሙያ ሲሰማራ ቢያንስ እነዚህን አምስት መርሆዎች ሊረዳና ሊያከብር ይገባዋል። እነሱም፦
1. እውነተኝነት እና ትክክለኝነት፣
2. ገለልተኝነት (ከፖለቲካ፣ ከኃይማኖትና ከሌሎች ሚዛንን ከሚያስቱ አቋሞች)፣
3. ፍትሐዊነት እና ሚዛናዊነት፣
4. ሰብአዊነት፣
5. ለሚሰራዉ ሥራ ተጠያቂነት
ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ ወዳስገደደኝ ጉዳይ ልመለስ። ኢትዮጵያ ውስጥ የጋዜጠኝነት ሙያና ሥነ-ምግባር ያለበትን ደረጃና ዝርዝር ታሪኩን በቅጡ የሚቃኝ ጥናታዊ ጽሑፍ የማቅረቡን ሥራ በሙያው ጥርሳቸውን ለነቀሉበትና አቅሙ ላላቸው ባለሙያዎች ልተውና የግል ትዝብቴን ላስቀምጥ። የወያኔ የአገዛዝ ሥርዓት በኢትዮጵያ ላይ ካደረሳቸው ትላልቅ ኪሳራዎች መካከል አንዱ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማዳፈኑ ነው። ይህን እኩይ ተልኮውንም ለማሳካት በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞችን በተለያዩ ጊዜያት እያሰረ፣ እየደበደበ፣ በሃሰት ክስ እየወነጀለና ከአገር እያሰደደ በማቆጥቆጥ ላይ የነበረውን የሕዝብ ነጻ የመወያያ መድርክ በጨቅላነቱ ቀጭቶታል። ወያኔ ነጻ የውይይት መድረኮችን ለማንጠፍ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። ጋዜጠኞችን በጸጥታ ኃይሎች ማዋከቡና በጡንቻው ማሸማቀቁ አልበቃ ብሎት ሕገ-መንግሥቱን የሚሽሩ ሕጎችንም ጭምር በማጽደቅ አፈናዉን ሕጋዊ አድርጎታል። ይህ አይነቱ በነጻ ሚዲያው ላይ ያነጣጠረው የማያባራ ዱላ ሕዝብ ነጻ የመወያያ መድርክ እንዳይኖረው ከማድርግም አልፎ መደማመጥና መተማመን የማይቻልበት የመጯጯህ ባህልንም ፍጥሯል። እውነትንና እውቀትን መሰረት ያደረጉ የሃሳብ መግለጫ መድረኮች እንዲከስሙ ተደርጎ በምትካቸው ጽንፍ የያዙና በሁለት አፋፍ ላይ ቆመው በጥላቻ፣ በሃሰት፣ ሰብአዊነት በጎደለውና ተጠያቂነት በማይስተዋልበት መንፈስ ውስጥ የተዋጡና ሕዝብን የሚያደናቁሩ የጩኸት መድረኮች ጎልተው እንዲወጡ ተደርጓል።
ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ መረጃ የሚያገኝበት እድል ሁለት ጽንፍ በያዙ እርስ በእርስ ተቃራኒ ነገር ግን ተመሳሳይ ባህሪይ በሚታይባቸው የፕሮፓጋንዳ መድረኮች እጅ ወድቋል። በአንድ ወገን “ልማታዊ ጋዜጠኞች” በግብር ከፋዩ ሕዝብ ገንዘብ በሚንቀሳቀሱትና ሙሉ በሙሉ የወያኔ ልሳን በሆኑት ቴሌቪዥንና ራዲዮ ጣቢያዎች፤ እንዲሁም ነጋ ጠባ ስለ አገዛዝ ሥርዓቱና ስለ ሹማምንቱ በጎ ገድል ብቻ ሲተርኩ የሚውሉ በግለሰቦችና በቡድን የተያዙ ሚዲያዎች (እንደ አይጋ ፎረም፣ ኢትዮጵያ ፈርስትና ሌሎችም)። በሌላኛው ጽንፍ ደግሞ “ሁለገብ ጋዜጠኞች” ለአገሩ በጎ አሳቢ በሆነውና በስደት በሚገኘው ኢትዮጵያዊ መዋጮ እና በፕ/ት ኢሳያስ አፎርቂ ወይም ሻቢያ ድጎማ የሚተዳደረው የግንቦት ሰባት ልሳን ኢሳት ቴሌቪዥንና ራዲዮ ጣቢያ፤ እንዲሁም ለተመሳሳይ ተልዕኮ በቆሙ ጥቂት ድኅረ-ገጾች ናቸው። በእነዚህ ሁለት ጽንፎች መካከል ከላይ የተጠቀሱትን የጋዜጠኝነት መርሆዎች በከፊልም ቢሆን ለማሳካት ካላቸው ቁርጠኝነት የተነሳ እውነተኛና ሚዛናዊ መረጃን ለሕዝብ ለማድረስ የሚተጉትን ሳንዘነጋ ጽንፍ የያዙት መድረኮች በመገናኛ ብዙሃን ስም በአገሪቱ የፖለቲካና ማኅበራዊ ሂደቶች ላይ እያደረሱ ያሉውን ከፍ ያለ ጉዳትና የሚያስከትሉትንም መዘዝ በቅጡ መፈተሽ የግድ ይላል።
ጽንፍ እንኳንስ ጥላቻን ለማራባት ይቅርና ፍቅርንም ለማጠንከር ቢሆን ውጤቱ አድጋ ነው። ጽንፍ ሚዛንን ያስታል፣ እውነትን እንዳናይ ይጋርዳል፣ ፍትሕን ያዛባል፣ ስብዕናን ያራቁታል፣ ለከባድ ስህተትና ውደቀትም ይዳርጋል። ጋዜጠኛም ጽንፍ የያዘ ዕለት ነገር ይበላሻል። እራሱን ብቻ ሳይሆን ድልድል ሆኖ የሚያቀራርበውንም ማህበረሰብ መንገድ ያስታል፣ ያናቁራል፣ ጥላቻ ያሰርጻል፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሆድና ጀርባ በማድረግ ለእልቂት ይጋብዛል። “ልማታዊ ጋዜጠኞች” እና አንዳንድ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሳይቀሩ የሆድ ነገር ሆኖባቸው ይሁን አምነውበት ከጥዋት እስከ ማት ወያኔ የሰራውንም ያልሰራውንም እያነሱና እየጣሉ፣ ተቃዋሚ ያሉትንም ሲያዋርዱና ሲያበሻቅጡ ስለሚውሉ ሕዝብ እንዲህ ያለውን ፕሮፓጋንዳ መስማት ታክቶታል። የሚረዳው አጣ እንጂ በድሃ አቅሙ ዲሺ እያስተከለ ፊቱን ወደ ውጭ ሚዲያዎች ሲያዞር ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ግልጽ ነበር። ውሸት መስማት ታከቶናል፣ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሰልችቶናል፣ አማራጭ አሳቦችንም መስማት እንፈልጋለን የሚል ነው። ወያኔ ሕዝብን ለመስማትም ሆነ ከስህተቱ ለመማር አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ ስለሌለው ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኖ ቀጥሏል። ወያኔ ሕዝብን አያዳምጥም፤ ሕዝቡም ወያኔን አያደምጥም።
በሕዝብና በአገዛዙ መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ለመጠቀም እድሉና አቅሙ የተፈጠረላቸው የኢሳት አይነት ሚዲያዎችም ሕዝብን ለማስተማርና ለማንቃት፤ እንዲሁም መብቱን ጠንቅቆ እንዲያውቅና ለነጻነቱም እንዲቆም ለማነሳሳት እድሉ ተፈጥሮላቸው ነበር። ይሁንና የኢሳት ተልኮም ሆነ አወቃቀር የግንቦት 7ን ሁለገብ የትግል ስልት መሰረት ያደረገ በመሆኑ በድርጅቱ ጠባብ አጀንዳና የትግል ስልት እንዲወሰን አስገድዶታል። “ሁለገብ” የሆኑ ጋዜጠኞችን አፍርቷል። ችግሩ ሁለገቦቹም ልማታዊ ጋዜጠኞቹ ተንደርድረው የወረደበትን ቁልቁለት ተከትለው አብረው መክነፋቸው ላይ ነው። ሕዝብ አማራጭ ስላጣ ዛሬን ሊሰማቸው ይችላል። አሁን ባሉብት ይዞታ ከቀጠሉ ግን ከሕዝብ ጋር መደማመጥ ይቀርና እንደ ወያኔ ሚዲያዎች በባዶ ሜዳ ማንቋረር ብቻ ይሆናል። ልማታዊ በሆኑት የወያኔ ጋዜጠኞችና ሁለገብ በሆኑት የግንቦት 7 ጋዜጠኞች መካከል ያለው አንድነትም ሆነ ሁለትነት ግልጽ ነው። ሁለቱም ለተለያዩ የፖለቲካ ተቋማት ልሳንነት ማገልገላቸው፣ ጠላት ብለው የፈረጁትን አካል የሚገልጹበት ያልተገራና ጨዋነት የጎደለው ቋንቋቸው፣ ወዳጅ የሆናቸውን ደግሞ ሽቅብ ሚከቡበትና የሚያሞካሹብት ስልታቸው፣ እንዲሁም በብዙ የፕሮግራምና የዜና አቀራረብ ስልታቸውም ጭምር አንድ አይነት እየሆኑ መምጣታቸው ነው። ሌላው ቢቀር አንዱ “አኬልዳማ” ብሎ የድራማ ፊልም ሲሰራ ሌላው “ኦፕሬሽን ሚሊኒየም” በሚል ከአዲስ አበባና ከአስመራ ያሰራጩትነ ዘገባ ልብ ይሉዋል።
ከላይ ከተጠቀሱት የጋዜጠኝነት መርሆዎች አንጻር ሁለቱንም በአንድ ጎራ ተሰልፈው እናያቸዋለን። ልማታዊዎቹ ጋዜጠኞች የወያኔን ባለሥልጣናትና የሻቢያን ተቃዋሚዎች ቅዱስ አድርገው በሚያቀርቡበትና በሚያሞካሹብት መጠነና ልክ ሁሉ ሁለገቦቹም ግንቦት 7ንና አጋሮቹን፤ እንዲሁም የሻቢያ ባለሥልጣናትን በተመሳሳይ ሁኔታ እያቀረቡ በሕዝብ ጉዳይና በፍትህ እንዲያላግጡና እንዲቧልቱ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ። ለዚህም በቅርቡ የግንቦት 7 ሹማምንትን አጅበው አስምራ የከረሙትን የኢሳት ጋዜጠኞች ቆይታ ልብ ይሉዋል። ልማታዊ ጋዜጠኞቹ የወያኔን ቱባ ባለሥልጣናት ተከትለውና የህውሃት አርማ ያለበትን መለዮ አጥልቀው የድርጅቱን 40ኛ ዓመት ለማክበር መቀሌ እንደ ከረሙት ሁሉ ሁለገቦቹ የኢሳት ጋዜጠኞችም ወታደራዊ ትጥቅና አልባሳትን አጥልቀው አስመራ በሚገኝ ሠራዊት መሃል እየተጎማለሉ የተነሱትን ፎቶና የቀዱትን ቪድዮ ላስረጂነት ማቅረብ ይቻላል።
ሰብአዊነትንም በተመለከተ በሁለቱም ጎራዎች የተሰለፉት “ጋዜጠኞች” ተመሳሳይ የመርህ ግድፈቶችን ሲፈጽሙ ማየት የተለመደ ነው። የዜጎቻቸውን መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች በመግፈፍ. አለም ያወቃቸውን አምባገነኖች እያሞካሹ፣ ወንጀላቸውን እየሸፋፈኑና የሌላቸውን ስብዕና እያለባበሱ ማቅረብ ፍትህን በሚናፍቁት ግፉአን ላይ እንደ ማላገጥ ነው የሚቆጠረው። መለስ ዜናዊንም ሆነ ኢሳያስ አፎርቂን ለሕዝቦቻቸው አሳቢና ባለ በጎ ራዕይ የአገር መሪዎች አድርገው ቢሚያቀርቡ ጋዜጠኞች መካከል ያለው ልዩነት የቆሙለት ወገንና ቦታ እንጂ የመርህ አይደለም። ለብዙ ንጹሃን ዜጎች ህይወት መጥፋት፣ ስቃይና እንግልት ቀጥተኛ ተጠያቂ የሆኑትን እነዚህ አንባገነኖች እየካቡ የፍትሕና የዲሞክራሲ ጠበቃ መሆን አይቻልም። በቅርቡ የኢሳት ጋዜጠኞች ፕ/ር ኢሳያስን ከራሳቸው ሕዝብ አልፈው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን የሚጨነቁ መሪ አድርገው ለማቅረብ ያደረጉት ሙከራ “የሁለገብ ታጋይነታቸው” ተልዕኮ መገለጫ እንጂ ከጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር የመነጨ አይሆንም። ባለፉት ሃያ አመታት ወያኔና ሻቢያ በሁለቱ አገራት ሕዝብ ላይ ሲፈጽሙት የቆዩትንና ዛሬም እየፈጸሙት ያለውን አስከፊ የሆነ የሰብአዊ መብቶች እረገጣ የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በተደጋጋሚ ያጋለጡባቸውን ሪፖርቶች እነዚህ “ጋዜጠኞች” የሚያዩበት መንገድም ሚዛኑን የሳተ ነው። ልማታዊዎቹ በወያኔ የሚፈጸመውን ጥሰት የሚያጋልጡትን የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በሰደቡበት አንደበታቸው እነዚህኑ ድርጅቶች እያጣቀሱ በኤርትራ ውስጥ ስለሚፈጸመው የመብት እረገጣ ሲተነትኑ በተደጋጋሚ ሰምቻለሁ። ሁለገቦቹ ጋዜጠኞችም የእነዚህን ድርጅቶች ሪፖርት እያጣቀሱ ወያኔ የሚፈጽመውን የመብት እረገጣ ማጋለጠቸው ይበል ቢያሰኝም ሻቢያ በኤርትራ ሕዝብና የሙያ አጋሮቻቸው በሆኑ ጋዜጠኞች ላይ ጭምር የሚፈጽመውን ግፍና በደል እንዳልሰሙ በመምሰልና ችላ በማለት ፕ/ር ኢሳያስን ለሕዝብ አሳቢና መልካም ስብዕና ያላቸው ሰው አድርገው ለማቅረብ መሞከራቸው የሌላኛው ጽንፍ ክሽፈት ነው።
ከላይ እንደገለጽኩት ክፉና አፋኝ የሆነ አንባገነናዊ ሥርዓት በአንድ አገር ውስጥ እረዘም ላለ ጊዜ ሥልጣን ተቆናጦ በሚቆይበት ወቅት ተመናምነው የሚጠፉ በርካታ እሴቶች እንዳሉ ሁሉ በምትካቸውም መጥፎና መረን የለቀቁ አዳዲስ ልማዶች ይፈለፈላሉ። አንዱ ይሄው መደማመጥ የሌለበት የመጯጯህ ባህል ነው። በ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የጀመረን ይህ ፈሊጥ ዛሬም አለቅ ብሎን ጽንፍ በያዙት በነዚህ መድረኮችም የተለያዩ ሃሳቦች አይንሸራሸሩም። በሃሳቦች ላይ ያተኮረ ውይይትና ክርክር የሚባል ነገርም የለም። ሁሉም የራሱን ብጤ ሰብስቦ ሌላኛውን ወገን ሲወቅጥ፣ ሲራገም፣ ሲያነሳና ሲጥል ነው የሚታየው። ተፎካካሪ ሃሳቦች በማይፋጩበትና በአንድ ጭብጥ ዙሪያ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውይይት በማያደርጉበት መድረክ ላይ አስር ተናጋራ አቅርቦ ሁሉም ባንድ ሙቀጫ ሌላውን የሚወቅጥ ከሆነ አንዳችም ጠብ የሚል ነገር የለውም። የአንድ ማኅበረሰብ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሊሰፋና ሊያድግ የሚችለው በሃሳቦች ዙሪያ በሚደረጉ ምሁራዊ ክርክሮችና ውይይቶች ነው። ጥላቻና ጽንፍ የተረጋጋና የሰለጠነ የፖለቲካ ማህበረሰብ እንዳይፈጠር ትልቅ እንቅፋቶች ናቸው። ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ ሽግግርም እንዳይፈጠር ያደርጋሉ። የፖለቲካ ጽንፍ በያዙ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩት የጥላቻና የሃሰት ዘገባዎች ቀጥተኛ ተጎጂው አገርና ሕዝብ ነው። የተጀመሩ የሰላማዊ ትግሎች ይኮላሻሉ። ንጹሃን ዜጎችም በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ተታለው ለአደጋ ይጋለጣሉ። ደግ ቀን ሲመጣ እናንተም ለትዝብት ትጋለጣላችሁና ከወዲሁ አስቡበት።
በቸር እንሰንብት!
ያሬድ ኃይለማርያም
http://ethioforum.org/amharic/%E1%8B%A8%E1%88%8D%E1%88%9B%E1%89%B3%E1%8B%8A-%E1%8A%A5%E1%8A%93-%E1%88%81%E1%88%88%E1%8C%88%E1%89%A5-%E1%8C%8B%E1%8B%9C%E1%8C%A0%E1%8A%9E%E1%89%BD-%E1%8A%A0/

No comments:

Post a Comment